- Debre Tabor
- Mar 25, 2024
- 2 min read
Updated: Apr 9, 2024
ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዮሐ3፦6
• ዳግመኛ ሰው እንዴት ሊወለድ ይችላል?
ሰው በጥምቀት ዳግመኛ ከእግዚአብሔር ልጅነትን በፀጋ ያገኛል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለው የአይሁድ መምህር ስለጥምቀት ባስተማረው ትምህርት እንዲህ ብሎአል፣ «ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳል ባህር ሲገስጽ ዛፍ ሲያናውጽ ድምጹን ትሰማዋለህ ነገር ግን የሚመጣበትን የሚሄበትን አታውቅም፤ ስለዚህ ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱበት ልደት እንዲህ ነው፡፡» ዮሐ 1፡1-9
• መቼ ነው የምንጠመቀው?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በሠላሳ /30 ዓመቱ/ ስለሆነ እኛም በሠላሳ ዓመታችን ዕድሜ/ መጠመቅ ይገባናል የሚሉ ይኖራሉ፡፤ የጌታ ደቀመዛሙርት ቅዱሳን ሐዋርያት በመንግሥተ ሰማያት ማን ይበልጣል በማለት በጠየቁት ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው አቁሞ ተመልሳችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም አላቸው፡፡/ማቴ 18፡1-6/ ደግሞም ሕጻናቱ ወደ ጌታ እንዳይቀርቡ ደቀመዛሙርቱ በከለከሉአቸው ጊዜ ሕፃናትን ተውአቸው ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና ብሎ እጁን ጭኖባቸው ባርኮአቸዋል፡፡ /ማቴ 19፡13-15/ ። እንግዲህ ይህ ሕፃናት ካላመኑ መጠመቅ አይገባቸውም የሚለውን ልማዳዊ አባባልን የሚቃወም ነው፡፡
ለማመንም ሆነ ላለማመን ያልበቁት ሕፃናት ወደ እርሱ እንዳይቀርቡ ደቀመዛሙርቱ በከለከሉአቸው ጊዜ ወደ እኔ እንዳይመጡ አትከልክሉአቸው ወደኔ ይምጡ በማለት ለምን ባረካቸው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክት፣ « እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ ማን ነው?» ብሎአል ( ሮሜ 8፡33- 34)። ስለዚህ ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀን ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀን እንዲጠመቁ ስትል ቤተክርስቲያን ወስናለች፡፡ ይህም እንዲሁ ሳሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረት በማድረግ ነው። ይኸውም አዳም በተፈጠረ በ40 ቀን ሔዋን በተፈጠረች በ 80 ቀን ሥላሴ ብርሃን አልብሰው ብርሃን አጎናጽፈው ልጅነትን ሰጥተው ገነት አግብተዋቸዋልና። ስለዚህ ነው /መጽሐፈ ኩፋሌ 4፡9/። ሌላው ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀን ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀን ይጠመቁ ስትል ቤተክርስቲን የወሰነችው። የወንድ መዋዕለ ንጽሕ/የመንጻት ቀን/ በ40 ቀን ሲሆን የሴት በ80 ቀን የሚፈጸም ስለሆነ ስለዚህ ነው።ዘሌ 12፡1-8/ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ምንም እንኳን በሌሎች ሴቶች ያለው ልማደ አንስት በእመቤታችን በቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ዘንድ የሌለ ቢሆንም እንደ ኦሪት ልማድና ወግ መዋዕለ ንጽሕ ሲፈጸም በ40ኛው ቀን ቤተመቅደስ ገብቶ በ40 ቀን ሊፈጸም የሚገባውን ኦሪታዊ ሥነ ሥርዓት ፈጽሟል፡፡ ጌታችን መምጣቱ ለትህትና ነው እንጂ ለልዕልና አይደለም። የእርሱ ግዝረት አስቀድሞ«በማህፀን ሳይገረዝ በመልአኩ» እንደተባለ መገንዘብ ይቻላል (ሉቃ 2፡21)። እንግዲህ መቼ መጠመቅ እንደሚገባን ከላይ ባጭሩ ከተገለጹት መገንዘብ ይቻላል። ቅድስት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንም በዚሁ መሰረት የምሥጢረ ጥምቀትን ሥርዓት ስትፈጽም የቆየች እንደመሆኗ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች፡፡